Skip to content

Resources Poetry

Ethiopian Poetry

Verse in Amharic — most of it short, four to eight lines, and set here line by line as it was written. Search a title or a phrase, read one poem at a time, or take one away as a card.

One of 161

ድንጋይ ዳቦ ነበር

ታውቂያለሽ የኔ ውድ

ድሮ በጥንት ዘመን እንደ አፈር ስንኖር

ስንዴ ብቻ ሳይሆን ድንጋይ ዳቦ ነበር

አሁን በኛ ዘመን ታሪክ ተቀይሯል

ድንጋይም ዘምኖ ዳቦነቱን ትቶ

ሰው መሆንን መርጧል

እና እንደነገርኩሽ

አፈር መሆን ትተው ድንጋይን ሚያስንቁ

ብዙ ሰወች አሉ ትውልድ የቀበሩ

ልንጠርባቸው ስንል አፈር ነን የሚሉ

ድንጋዮች በዝተዋል ሰውን የመሰሉ

161 poems

All poems

  • እግዜርን አግኝቸው

    እግዜርን አግኝቸው እንዴት በነገርኩት

    አምላኬን አግንቼ እንዴት በነገርኩት

    ፈጣሪን አግንቼ እንዴት በነገርኩት

    የደላኝ መሰለው ተመስገን ስላልኩት።

  • ተይ ወሼ ተይ ወሼ

    ኧረ ዋንዛም ነበርኩ

    ኧረ ዝግባም ነበርኩ

    ኧረ ወይራም ነበርኩ

    ቆረጡኝ ተቆረጥኩ

    አነደዱኝ ነደድኩ

    አከሰሉኝ ከሰልኩ

    አመድ ሆንኩላቸው

    ከጓሯቸው ደፉኝ

    አህያቸው ቃመኝ

    ኧረ ተይ አትቃሚኝ

    ተይ ወሼ

    ተይ ወሼ

    ሰው የሆንኩኝ እንደሁ ዳግም ተመልሼ

  • እድል

    ሰው ሰለፈለገ ብቻ አያገኝም

    ስላልጠየቀም አያጣ!

    እድል ፍትህ የላትም

    ምኞት ከበጋ ካፊያ

    ተስፋ ከጤዛ ያጥራል

    ሲለው ይጠማል ሲለው ይሞላል

    ለአመታት የለመኑትን ነስቶ

    ማለዳ የጠየቁትን ያድላል

  • የናፍቆት ርሃቤ

    ትዝ ይለሻል ፍቅሬ?

    ያኔ አብረን እያለን በፍቅር ተሳስረን

    ምሽት በጨረቃ በደስታ ሰክረን

    ወገቤን አቅፈሽኝ አንገትሽን ጠምዝዤ

    ቁልቁል አይንሽን ሳይ አንገቴን አዝምሜ

    በጨረቃ ብርሃን በከዋክብት ደምቀን

    በዚያ ውብ ምሽት አምረን አሸብርቀን

    በፍቅር አማልክት ዙሪያውን ተከበን

    እንደ ፅጌሬዳ አምሮብን ተውበን

    ያሳለፍነው ጊዜ እየመጣ ባይኔ

    ዛሬ ጎኔ ሳጣሽ ሆነብኝ ምናኔ

    በምሽት ብቻየን ጨረቃዋን ሳያት

    ፍቅርን ባየንበት በለመድነው ሰዓት

    አብረሽኝ እንዳለሽ ሁሌም ይሰማኛል

    የቀን ትዝታየን ጭንቄን ያስረሳኛል

    ዛሬስ ጨረቃዋም በኔ ላይ ጨከነች

    ሰአቷን ጠብቃ አልወጣልኝ አለች

    በጥቁር ደመና በፅልመት ተውጣ

    የናፍቆት ርሃቤን አስቀረችው ውጣ።

  • ፍቅር አፍ አወጣ

    ፍቅር አፍ አውጥቶ ዛሬ ተናገረ

    የጥላቻም ድልድይ ይሄው ተሰበረ

    አፋችን ነው እንጂ ልባችን አንድ ነው

    ባለማወቅ ነበር ድሮም ያጠፋነው

  • ሰው አትውደድ ልቤ

    ሰው አትውደድ ፣ ልቤ ይብቃህ

    የመውደድን እጣ መቸም አላደለህ

    በፍለጋ አትገኝ አትመጣ በጥሪ

    አሁን የት ተገኝታ የልብ ተፈቃሪ

  • ዝም መጫወቻ

    ባዶ ቤት በክረምት

    አንች የሌለሽበት

    ዝም ጸጥ ብቻ

    ጣሪያ መጫወቻ።

    አመሻሽ

    ኦና ቤት

    አንች የሌለሽበት

    ፀጥ-ረጭ ፣ ብቻ

    ወለል መጫወቻ።

    ጠረንጴዛ

    ወንበር

    አንድ አልጋ

    አንድ በር

    አንድ እኔ

    አንድ መስኮት

    ባዶ ቤት

    በክረምት

    አንች የሌለሽበት

    ፀጥ-ረጭ ብቻ

    እም መጫወቻ

    ዝም መደሰቻ

    ዝም ዝም

    ዝም ዝም

    ዝም ዝም ለብቻ።

  • ወይ ጨልሞ አልቀረ

    ወይ ጨልሞ አልቀረ ፤ አሊያ ደግሞ አልነጋ

    እንዲህ እኖራለሁ ፤ መንፈሴ ሳይረጋ

    የአህያ ሆድ መስሎ ፤ ከቦኝ የጅብ መንጋ።

  • ቅዠት

    በጀርባዬ ተንጋልዬ

    ሄደ ሰማዩን ቀዶ ህሊናዬ

    በቅጽበት የፈተልኩትን ለብሼ፣ ሞቆኝ

    በኔው ዓለም እኔው ነግሼ፣ ደልቶኝ

    ከጽድቁ ገበታ ቀምሼ፣ ጣፍጦኝ

    ቀና ብል …

    ያቻት ጎጂዬ ደብዝዛ

    እንደ ክፉ ቀን ቀዝቅዛ

    ንፉግ ፍቅሯን ለማየቱ

    ብርሃን እንኳን መታጣቱ

  • ታጠበ ሸሚዜ

    እኔ ልሙትልሽ እያልኩኝ አልምልም

    ቃላትን መንዝሬ ለሞት ቀብድ አልከፍልም

    እራሴን እንዳጠፋ በረኪና የላክሽልኝ ጊዜ

    እድሜ ለስጦታሽ ታጠበ ሸሚዜ።

  • አትንፈገኝ ጌታ

    ውበትና ገንዘብ የጠዋት ጤዛ ነው

    ማማር መጠበብም እስካሉ ድረስ ነው

    ጓደኛም ይቅርብኝ ጊዜ ይለውጠዋል

    መወደድ ከንቱ ነው ወረት ይንደዋል

    ነፍሴ በመንግስትህ እንዳታጣ ቦታ

    ለልቤ ቅንነት አትንፈገኝ ጌታ

  • ተይ ስሚኝ ሀገሬ

    ከፍ አልን ስንል፣ እያሳነሰ

    ተራ በተራ እየቀነሰ

    ቅዠት ሊያደርገው ታላቅ ህልምሽን

    ጠባብ ጨረሰው ሰፊው ህዝብሽን